Faith Foundation

webpic_homepage2

የኬኤልሲ የእምነት መግለጫ

 

በኪንግደም ላይፍ ሴንተር (በኬኤልሲ) የምናምንባቸው እና አጥብቀን የምንከተላቸው ሁሉንም እንቅስቃሴያችንን እና አቋማችንን የሚወስኑ የእግዚአብሔር መንግስት መርሆች እነዚህ ናቸው::

 • ስልሳ ስድስቱን መጻሕፍት የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እስትንፋስ የሆነ ህያው ቃል፣ የሚሰራ፣ ለዘላለም የሚኖር፣ ፈጽሞ ስሕተት የሌለበት፣ የእግዚአብሔርን ፍቃድ እና ሃሳቡን ለማስፈጸም ከፍተኛ እና ሙሉ ስልጣን ያለው ነው:: የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ዓላማ ወደ ፍጻሜ ለማምጣት የሚያስችልና: ሰዎችን በእውነትና በትክክለኛ ስነምግባር ለማነጽ የእውነት መርሆችን የያዘ ሙሉ መጽሐፍ ነው::
 • ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖር አንድ አምላክ እግዚአብሔር በሦስትነት የተገለጠ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ የሚታየውን እና የማይታየውን የፈጠረ የሁሉ ነገር አስገኚ ሲሆን በፍጥረት ሁሉ ላይ ፍጹም ገዢ ነው::
 • የሰው ዘር ከመጀመሪያው በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠረው ማንነቱ ባለመታዘዝ ምክንያት ወድቋል:: ከዚህም የተነሳ የሰው ልጅ ንስሃ ገብቶ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራውን ሙሉ ስራ ቢያምን ይድናል: የማያምን ደግሞ የዘላለም ፍርድ ይጠብቀዋል::
 • ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶ ከድንግል ማሪያም ተወልዶ የሰው ልጆችን የማዳን ስራ የፈጸመ ፍጹም አምላክ እና ፍጹም ሰው ነው::
 • ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ኃጢያት እንደሞተ እና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደተነሳ: ለደቀ መዛሙርቱም እንደታየና ወደ አባቱም እንዳረገ: ቤተክርስቲያንን ሊወስድ ከቅዱሳኑ ጋር ተመልሶ በክብር ይመጣል::
 • የውሃ ጥምቀት፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት፣ በልሳን መናገር፣ መለኮታዊ ፈውስ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ቤተክርስቲያን ልትለማመዳቸው የሚገቡ እውነቶች ናቸው::
 • መንፈስ ቅዱስ በአማኝ ውስጥ በመኖር አማኙ የክርስቶስን የባህሪ ፍሬ እንዲያፈራ ያስችለዋል:: መንፈስ ቅዱስ እንደ እግዚአብሔር ቃል መሰረት ለእያንዳንዱ አማኝ መንገድ ያሳያል፣ ያስተምራል፣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራል:: በጋራ ደግሞ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን ፍቃድ እና ዓላማ መፈጸም እንድትችል ስጦታዎችን እና ጸጋን ይሰጣል::
 • ቤተክርስቲያን የተገነባችው በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ አማኞች በአንድነት በመያያዝ አንድ መንፈሳዊ አካል በመሆን ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ሕዝብ ለመሆን ነው:: ዘላለማዊው አምላክ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር ለዘላለም እንድትገዛ ወስኗል::
 • የሐዋርያት ስራ መጽሐፍ ከተጻፈበት ጊዜ ብዙም ሳይቆይ ቤተክርስቲያን እውነተኛውን እምነት በመተው ወደባህላዊ ሃይማኖት ገባች:: ከዚያም ምንም እንኳን በሃይማኖታዊው መንገድ ወደፊት ብትገፋም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት በመራቅ ወይም በተሳሳተ መልኩ በመረዳት የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ መንገድ በስራ ላይ አውላለች:: ስለዚህ አሁን ቤተክርስቲያን በጉዞ ላይ ነች። በዚህም ጉዞ አማካኝነት እውነትን ሁሉ በማስመለስ እና በመግለጽ በተጨማሪም ብትክክለኛ መረዳት እና በብቃት እንዲሁም በአማኞችም መጨመር እየተገነባች ነው::
 • የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የአገልግሎት ስጦታዎች ማለትም ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ ወንጌላውያን፣እረኞች እና አስተማሪዎች ዛሬም እንደሚሰሩ እና ቤተክርስቲያንን ለመገንባት እና ቅዱሳንን ለአገልግሎት ስራ ለማዘጋጀት በክርስቶስ ኢየሱስ ለቤተክርስቲያን ተሰጥተዋል:: ያለ እነዚህ አገልግሎቶች ቤተክርስቲያን ወደ ፍጻሜ መድረስ አትችልም::
 • እግዚአብሔር ለሐዋርያት እና ለነቢያት ከሰጣቸው የመገንባት፣ የማየት፣ መለኮታዊ ጥበብ የመቀበል እና የማወጅ ጸጋ ቤተክርስቲያንን በእውነት መሰረት ላይ ይገነባሉ:: የዚህ ግንባታ መጨረሻው የቤተክርስቲያን ወደ ሙሉነት መድረስ እና የክርስቶስን ባህሪ በመኖር የክርስቶስን በአካል መመለስ እና ይህ የሚበሰብሰው አካል የማይበሰብሰውን ማንነት መልበስነው:: ይህንን እውነት ወደ ፍጻሜ ለማምጣት እግዚአብሔር የታደሰ መረዳት እና ማንነት ያለውን ከዚህ ዘመን የተበላሸ ሕይወት የራቀ ንጹህ ልብ ያለውን አዲስ ሰው እየገነባ ነው::
 • የቤተክርስቲያን ወደ እውነት መመለስ እና ትክክለኛ ባህሪን የመገንባት ስራ ሂደት: በቤተክርስቲያን ውስጥም ሆነ ከቤተክርስቲያን ውጪ በሚሰራው በማይታየው የዚህ ዓለም ኃይላት እና ስልጣናት ተቃውሞ አለበት:: እነዚህን ኃይላት እና ስልጣናት ልንቋቋማቸው እና ልናሸንፋቸው ይገባል:: ትልቁ የጠላት ስልት በቤተክርስቲያን ውስጥ የሞተና ልምዳዊ የሆነ ባህላዊ ሃይማኖትን በመመስረት እና ቤተክርስቲያንን በተበላሸ እሴት በመውረር ትክክለኛ የሆነውን አገልግሎት ማዛባት ነው:: ጉዞው እስካልተፈጸመ ድረስ ክርስቶስ ተመልሶ አይመጣም:: ስለዚህ ቤተክርስቲያን ልትዘጋጅ እና ሁሉንም ጠላቶቿን ድል መንሳት አለባት::
 • ቤተክርስቲያን በዚህ ምድር መንግስታት ላይ ተጽእኖ ልታመጣና በእግዚአብሔር መንግስት መርህ ምድርን እንድትመራ በእግዚአብሔር ትንቢታዊ ቃል የተነገረ ስልጣን ተሰጥቷታል:: የእግዚአብሔርን ስራ ለማድረግ እና ፍቃዱን ወደ ፍጻሜ ለማምጣት ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ልትተባበር ይገባታል:: ይህ ትብብር ደግሞ የእኛ ተሳትፎ ያለበት እና እግዚአብሔር ራሱ እንደሚፈልገው: ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት: በራሱ መንገድ መንግስቱን ለማስቀደም የእርሱን ምሪት የተከተለ መሆን ይገባዋል::
 • የእግዚአብሔር መንግስት ይበልጥ ወደፊት ሊቀድም የሚችለው የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል በማወጅ እና ያንን የታወጀውን ቃል ወደ ሰው ልብ ውስጥ እንዲታተም በማድረግ እንዲሁም ይህ ቃል የሚፈለገውን ትክክለኛ የአኗኗር ዘይቤ እና ፍሬ ያለው ሕይወትን ሲያስገኝ ነው::